ቀጥታ፡

የመዲናዋ የወንዝ ዳር ልማቶች የወንዞች ደህንነት እንዲጠበቅ ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተከናወኑት የወንዝ ዳር ልማቶች ከህዝብ መዝናኛነታቸው ባሻገር የወንዞች ደህንነት እንዲጠበቅ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ከወንዞች ጋር በማገናኘት ሲፈጠሩ በቆዩ ችግሮች ወንዞች ለብክለት ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡

ይህም ወንዞቹ ለሰዎች፣ ለእንስሳትና ለዕፅዋት ጤንነትና ደህንነት ጥቅም ከመስጠት ይልቅ ስጋት እንዲሆኑ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡

ይህን ተከትሎ በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አድማሱን በማስፋት ወደ ወንዝ ዳርቻ ልማት በመሸጋገሩ የወንዞችን ደህንነት ማስጠበቅ ተችሏል፡፡

የወንዝ ዳር ፕሮጀክት መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የስጋት ምንጭ የነበሩት ወንዞች የመዝናኛ ማዕከል ሆነዋል፡፡

ኢዜአ በወንዝ ዳር ልማቶች በለሙ ቦታዎች ሲዝናኑ ያገኛቸው የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች እንደገለጹት ቦታዎቹ አማራጭ የእረፍት ማሳለፊያ ከመሆናቸው ባሻገር የከተማዋን ገጽታ ውብ አድርገውታል፡፡

አቶ መርሳ በቀለ በወንዞች ዳርቻ የተሰሩ የልማት ስራዎች ከዚህ ቀደም ለማየትም ሆነ በአካባቢው ለማለፍ አስቸጋሪ የነበሩ ቦታዎችን ውብና ጽዱ ያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ወንዞችን ከብክለት ነፃ በማድረግ ደህንነታቸው ተጠብቆ ለህዝብ መዝናኛነት እንዲውሉ ከማስቻል ባለፈ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ጽዱ እንዳደረጓት ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ግርማዬ ፍስሃ በበኩላቸው፤ የከተማዋ ወንዞች የቆሻሻ መጣያ እንደነበሩ አስታውሰው፤ በዚህ ደረጃ ለምተው በመመልከታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የልማት ስራው ወንዞቹንና በዙሪያቸው ያሉ አካባቢዎችን ውብና ፅዱ ከማድረግ ባሻገር ኢትዮጵያዊያን በአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ልምድና ክህሎት ያሳዩበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ጋዲሳ ዋቅጅራናቸው፡፡

በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች ለህፃናትና ወጣቶች የሚያገለግሉ ምቹ የሆኑ በርካታ መዝናኛዎች መገንባታቸውን የተናገሩት ወጣት ሰለሞን ዳዊት እና አብዲ መልካሙ ናቸው፡፡

መዝናኛ ቦታዎቹ ጊዜአችንን በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይልቅ በመልካም ድባብ በመታጀብ ንፁህ አየር እየወሰድን እንድንዝናና ዕድል ፈጥረውልናል ብለዋል፡፡

የልማት ስራዎቹ ከመዝናኛነት ባለፈ ህብረተሰቡ ስለ አካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር የሚያስችሉ መሆናቸውን የገለጸው ወጣት ይታያል ደጋጋ ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም