ቀጥታ፡

በክልሉ በክረምቱ ወራት ለተተከሉ ችግኞች በበጋው ወራት የሚደረገው እንክብካቤ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ጋምቤላ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከቡ ስራ በበጋው ወራትም ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ገለፀ።

የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አንድሪው ቱት ለኢዜአ እንደገለፁት በክረምቱ ወራት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከቡ ስራ በበጋውም ወራት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ህብረተሰቡ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የጽድቀት መጠናቸው እንዲጨምር እንክብካቤ እንዲያደርግ ግንዛቤ መፈጠሩን አንስተዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ የለሙ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ይዞታቸው እንዲመለሱ የእንክብካቤና የጥበቃ ስራው እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ የለሙ አካባቢዎችን በመጠበቅ ለስራ እድል ፈጠራ እንዲውሉ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች  መተላለፋቸውንም ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ ከስራ ዕድል ፈጠራው ባለፈም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርታማነት በመጨመር የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለአብነትም ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው የማንጎ፣ የፓፓያ፣ የሙዝና ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች የአርሶ አደሩን ህይወት መለወጥ መጀመራቸውን ገልፀዋል።


 

በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ዳይሬክተር ኬት ሉል በበኩላቸው በክልሉ በክረምቱ ወራት በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ችግኞች ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ እንዲሁም ከሰደድ እሳት በመጠበቅና ለመንከባከብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለተግባራዊነቱ ስራ አጥ ዜጎችን በማደራጀት ችግኞችን በመንከባከብ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው የክረምት ወራት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠንም 78 በመቶ መድረሱን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም