ቀጥታ፡

የኢትዮ-ሳዑዲ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተና በተጨባጭ ውጤቶች የታጀበ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ሳዑዲ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተና በተጨባጭ ውጤቶች የታጀበ ነው ሲሉ በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ ዘመናትን የተሻገረ የባህል፣ የሃይማኖትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ቅርጽ መያዙን አስታውሰው፤ አሁን ላለው ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሰረት እንደጣለም ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በማህበራዊ መስተጋብር እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡

በተለይ ከለውጡ ወዲህ የሀገራቱ ሁለንተናዊ አጋርነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማደጉን ጠቁመው፤ በዚህም በርካታ የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የግብርና ምርቶችን ወደ ሳዑዲ እንደምትልክ ተናግረው፤ የሁለቱ ሀገራት ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተና በተጨባጭ ውጤቶች የታጀበ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት በርካታ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ 200ሺህ ኢትዮጵያውያን በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገሪቱ መግባታቸውን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት 360ሺህ ዜጎችን ለመላክ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

በቀጣይም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩንና ሁለንተናዊ ግንኙነትን የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም