የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በኢንስቲትዩቱ ምርትና ምርታማነትን ማረጋጋጥ የሚያስችሉ ውጤታማ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋና የሰው ኃይል በመጠቀም የምግብ ዋስትናንና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ እንዲሁም የአሰራር ማሻሻያዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሰብል ዝርያዎች ላይ በተከናወኑ የምርምር ስራዎች የጤፍ ምርታማነት በእጥፍ ማደጉን ጠቅሰው የስንዴ ምርታማነት በሄክታር ከ12 ኩንታል ወደ 36 ኩንታል መድረሱን አስረድተዋል።
በተመሰሳይ ከአንድ ሄክታር ይገኝ የነበረውን 20 ኩንታል የበቆሎ ምርት አሁን ላይ 45 ኩንታል ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም ከአንድ ሄክታር ይሰበሰብ የነበረውን 8 ኩንታል የቡና ምርት አሁን ላይ 28 ኩንታል ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያከናወነቻቸው ያሉ መርኃ ግብሮች ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ በኢንስቲትዩቱ የሚከናወኑ ምርምሮች ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለማፍለቅ እንዲሁም ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል የጤፍ ዝርያ ማፍለቅ የሚያስችል ምርምር በሙከራ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
የምርምሩን ውጤት በአርሶ አደር ማሳ ላይ በመሞከር በቀጣይ ለማስፋፋት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ ግኝቱ የጤፍ ምርታማነትን በእጥፍ ያሳድገዋል ብለዋል።