ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ይመለሳል።

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻለም። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። ስድስት ግቦችን ሲያሳርፍ 10 ግቦች ተቆጥረውበታል።

መቀሌ 70 እንደርታ በሁለት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ጨዋታው ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት ለማጠናከር መቀሌ 70 እንደርታ በውድድር ‘መቱ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዘገብ የሚያደርጉት ነው።

በሌላኛው መርሃ ግብር ነጌሌ አርሲ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 10 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። ቡድኑ በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አራት ጎሎችን አስተናግዷል።

ነጌሌ አርሲ ከአምስቱ ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ በማግኘት 15ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል።

ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ምንም ግብ አላስተናገደም። ቡድኑ በዘጠኝ ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ህዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ጨዋታቸውን ያደረጉ ክለቦች ከስድስተኛ እስከ ዘጠነኛ ሳምንት በሃዋሳ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሃዋሳ ጨዋታቸውን ያደረጉ ክለቦች በአዲስ አበባ እንደሚጫወቱ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው እና የሃዋሳ ከተማው ያሬድ ብሩክ በተመሳሳይ አራት ግቦች እየመሩ ነው። የሃዋሳ ከተማው ጌታነህ ከበደ፣ የፋሲል ከነማው በረከት ግዛው እና መሐመድ አበራ ከመቻል በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም