ቀጥታ፡

የተረከብናቸው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች ግለሰቦች በእጃቸው የሚገኙ ቅርሶችን እንዲመልሱ የሚያበረታታ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2018(ኢዜአ)፦ ዛሬ ከጀርመናውያን ቤተሰቦች የተረከብናቸው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች በተመሳሳይ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች በእጃቸው የሚገኙ ቅርሶችን እንዲመልሱ የሚያበረታታ ነው ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለፁ።

በጀርመናውያን ቤተሰቦች እጅ የነበሩ 12 ልዩ ልዩ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተረክቧል፡፡


 

በርክክብ ስነ ስርዓቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙዔል ክፍሌ(ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ፈርዲናንድ ቮን ወይሄ(ዶ/ር) ተገኝተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ቅርሶች እኤአ 1921-1928 በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ ለነበሩት ፈርቲዝ ዌይስ በንግስት ዘውዲቱ እና አጼ ኃይለሥላሴ በስጦታ ተበርክተው የነበሩ እና በግል የተገዙ ናቸው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በህይወት የሌሉት የፈርቲዝ ዌይስ የልጅ ልጅ ራሞርና ቤተሰቦቹ በራሳቸው ተነሳሽነት በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ በኩል ጥንታዊ ቅርሶቹን መልሰዋል ነው ያሉት፡፡

ቅርሶቹ ከቱሪዝም መስህብነታቸው ባሻገር ታሪክን ወደ ቤቱ የመለሱና የሀገራቱን ወዳጅነት በግልጽ ያሳየ መሆኑን ጠቁመው፤ ድርጊቱ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች በእጃቸው የሚገኙ ቅርሶችን እንዲመልሱ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባበቂ ፕሬዚዳንት ሳሙዔል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በስጦታ የተበረከቱም ሆነ የተወሰዱ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርሶችን እንዲመለሱ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ፈርዲናንድ ቮን ወይሄ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቅርሶቹ የተመለሱት ያለምንም ጣልቃ ገብነት በቅርሱ ባለቤት ቤተሰቦች መልካም ፈቃድ ነው ብለዋል፡፡

ይህም የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡


 

ከተመለሱት ቅርሶች መካከል ጎራዴ፣ ዘውድ፣ አክሊል፣ ስዕሎችና ሌሎች የኢትዮጵያን ማንነት የሚገልጹ ቅርሶች እንደሚገኙበት የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዮሃንስ አድገህ(ዶ/ር) ናቸው።

ቅርሶቹ ከቱሪዝም መስህብነት ባሻገር ለጥናትና ምርምር ግብዓት ሆነው እንደሚያገለግሉም ተናግረዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ፍርቲዝ ዌይስ የልጅ ልጅ ፕሮፌሰር ራሞን ዌይስ በበኩላቸው፤ ቅርሶቹ ከግለሰብ ይልቅ ለኢትዮጵያ ይበልጥ ይጠቅማሉ ብለን እንደቤተሰብ መክረን መልሰናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም