አመራሩ በመፍጠር እና በመፍጠን ለልማትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ በመፍጠር እና በመፍጠን ለልማትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል
አሶሳ፤ ህዳር 10/2018(ኢዜአ)፦ በየደረጃው ያለው አመራር በመፍጠር እና በመፍጠን ለሀገር ልማትና ለህዝብ ተጠቃሚነት በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር ተናገሩ።
ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች "በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እምርታ" በሚል መሪ ሃሳብ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር፤ የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት ለማስቀጠል በተለይም የአመራሩ ብቃትና ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በየደረጃው ያለው አመራር በመፍጠር እና በመፍጠን ለሀገር ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት የበለጠ ለመስራት ሊዘጋጅ እንደሚገባ አስገንዝበው የስልጠናው አላማም ይሄው ነው ብለዋል።
በስልጠናው የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም፣ የከተማ ልማት እና ሌሎች ዘርፎች ላይ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ለማስቀጠል የዳበረ ውይይት የሚደረግበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በስልጠናው ተሞክሮዎችና ልምዶችን በመጋራት አመራሩ በጋራ ለላቀ ስኬት ለመስራት የሚዘጋጅበት ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የአመራሮቹ ስልጠና ለተከታታይ ስምንት ቀናት የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል።