አመራሩ የአስተሳሰብ አንድነትን እንዲሁም የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ የአስተሳሰብ አንድነትን እንዲሁም የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2018(ኢዜአ)፦ የአመራሩን የአስተሳሰብ አንድነት እንዲሁም የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠራ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት ሁለተኛ ዙር የከፍተኛና መካከለኛ የአመራር አባላት ስልጠና በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በስልጠናው የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ስልጠናው “በመደመር መንግሥት እይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ለሚቀጥሉት ስምንት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሞገስ ባልቻ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ገለጻ፤ የአመራሩን የአስተሳሰብ አንድነት እንዲሁም የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
አመራሩ የአስተሳሰብ አንድነትን እንዲሁም የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ማጠናከር እንደሚገባውን ተናግረዋል።
የስልጠናው ዓላማም በአመራሩ መካከል የበለጠ መቀራረብና የአስተሳሰብ አንድነትን መፍጠር እንዲሁም የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ማጎልበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አገልጋይና ሁለገብ የሆነ አመራር መፍጠር ከስልጠናው ዓላማዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
ስልጠናው በተለያዩ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በማተኮር እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በዚህም ስልጠናው በመደመር መንግስት እይታ የግብርና፣ የገጠር፣ የመዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ጉዞ፣ የኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም ዘርፍ እመርታ እንዲሁም የከተማ ልማት በሚል ርዕሶች ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው የአመራሩን እውቀት፣ ክህሎትና አቅም የሚገነባ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ከሁለት ሺህ በላይ የፌዴራልና የከተማዋ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር አባላት እንደሚሳተፉና ጎን ለጎንም የተግባርና የመስክ የልማት ስራ ጉብኝቶች እንደሚከናወኑ ተገልጿል።