በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነር ስልጠናዎች ችግር ፈቺ ፈጠራና መፍትሔዎችን እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነር ስልጠናዎች ችግር ፈቺ ፈጠራና መፍትሔዎችን እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነር ስልጠናዎች ችግር ፈቺ ፈጠራና መፍትሔዎችን እያስገኙ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡
የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንትን በማስመልከት የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት የኢንተርፕርነርሽፕ ስነ ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢንተርፕርነርሽፕ ሥነ ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችሉ አሰራሮችና ተቋማት ሪፎርምና አጀንዳ ቀረፃ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መንግስት በመፍጠርና በመፍጠን አገልግሎቶችን በመስጠት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከተቋቋመ ጀምሮ የኢንተርፕርነር ስልጠናዎች ከግለሰብ እስከ ተቋማት ድረስ እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ኢንተርፕርነሮችን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁና ንቁ ተወዳዳሪ በማድረግ ሀገራቸውን ከድህነት የሚያወጡ ዜጎችን ማፍራት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
የኢንተርፕርነር ስልጠናዎች ችግርን መሰረት ያደረጉ መፍትሄ ሰጪ ፈጠራዎችን እያስገኙ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት ኢትዮጵያን የምንገነባበትና ወደ ፊት የምናስፈነጥርበት፤ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ለማድረስ የምንጠቀምበት መድረክ ነው ሲሉም ገልዋል፡፡