በመረጃ ላይ የተመሰረተና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመረጃ ላይ የተመሰረተና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2018(ኢዜአ)፦ በመረጃ ላይ የተመሰረተና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እየተሰጠ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ቴሬሳ ገለጹ፡፡
የውጭ ሀገራት በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሥራ ስምሪት የሚያገኙ ሴቶችን ጤናና ደህንነት ጥበቃ በተመለከተ በተዘጋጀው "ኢኖቬት" የተሰኘ የአራት ዓመት ፕሮጀክት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ቴሬሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት የሚያገኙ ዜጎች በጥናትና መረጃ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ያስችላል፡፡
በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚሰማሩ ዜጎች ጤና ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ የዜጎችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ዋና ትኩረቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሪፎርሙ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን በመረጃ ላይ ወደ ተመሰረተ የአሰራር ስርዓት ለመቀየር ዲጂታል ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት የሪፎርሙ አካል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የመረጃ ስርዓቱ ግልጽ፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበትና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የሚፈጥር የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት መስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተገቢ የሙያ ድጋፍ፣ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ፈጣን የቆንስላና የማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል፡፡
የ"ኢኖቬት" ፕሮጀክት አስተባባሪ ካሳሁን ሀብታሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሥራ ስምሪት የሚያገኙ ሴቶች ደህንነትና ጤና ማሻሻል ላይ በማተኮር ለውጤታማ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዜጎች ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ስልጠና መስጠት፣ በተሰማሩበት ሀገራት ሆነው መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ የእርስ መርስ መደጋገፍን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፕሮጀክቱ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የጽሁፍና የድምጽ መረጃዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮች ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የፕሮጀክቱ ተወካይ ሳምራዊት ሰለሞን (ዶ/ር) በውጭ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ሴቶች የስነ አዕምሮ፣ የስነ ተዋልዶና ሌሎች የጤና መረጃዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጀርመን ሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ የኮፒውቲንግ እና ዳታ ሳይንስ ማእከል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማርቲን ሴማን (ዶ/ር) የዜጎችን ደህንት ማስጠበቅ በተናጠል የሚሰራ አይደለም ብለዋል፡፡
"ኢኖቬት" የተሰኘው ፕሮጀክትም ቅንጅትን መሰረተ በማድረግ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ መስራተ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡