ቀጥታ፡

የህዝብን ሰላም በማስጠበቅና ለልማት ስራዎች ስኬታማነት በላቀ ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንሰራለን- የፖሊስ አባላት

ቦንጋ፤ ህዳር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የህዝብን ሰላም በማስጠበቅና ለልማት ስራዎች ስኬታማነት በላቀ ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፖሊስ አመራርና አባላት ተናገሩ።

በክልሉ "ከጂኦ ስትራቴጂካዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና" በሚል መሪ ሃሳብ በየደረጃው ለሚገኙ የፖሊስ አመራርና አባላት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

በስልጠናው ላይ የተሳተፉ የፖሊስ አመራርና አባላትም የተሰጠው ስልጠና በላቀ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ህዝብን ከማገልገል ባለፈ በሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመያዝ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የህዝብን ሰላም በማስጠበቅና ለልማት ስራዎች ስኬታማነት በላቀ ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ኮማንደር እታለማው ተፈራ፣ ኢንስፔክተር አባይነህ አልዬ እና ምክትል ኢንስፔክተር አንድነት አበራ፤ የተሰጠው ስልጠና ወቅታዊ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮችን በመረዳት ለላቀ ህዝባዊ አገልግሎት የሚያዘጋጅ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመረዳት በዚሁ ልክ የፓሊስ አባላት አቅማችንን ማሳደግ ያለብን መሆኑን የተገነዘብንበት ነው ብለዋል።

በሁሉም መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ከምንም በላይ የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አንስተው ለዚህም የፖሊስ አባላት የላቀ ሃላፊነት ይጠበቅብናል ለዚህም ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።

የህዝብን ሰላም በማስጠበቅና ለልማት ስራዎች ስኬታማነት በላቀ ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንሰራለን በማለትም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ የፖሊስ አባላት የህዝብና የሀገር ወገንተኝነታቸውን በተግባር በማሳየት ለሰላምና ለልማት ዘብ መቆም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተመዘገበው ስኬት ውስጥ የፖሊስ ድርሻ የላቀ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ይህንኑ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የበለጸገችና ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር በመገንባት ሂደት በየሙያ መስኩ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አንስተው የፖሊስ አባላት የክልሉን ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስቀጠል እንዲተጉ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት የፖሊስን አቅም በቴክኖሎጂ እና በስልጠና ጭምር ለማጠናከር የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተሰጠው ስልጠና ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳ እና ከከተሞች የተወጣጡ የፖሊስ አባላትና አመራሮች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም