ቀጥታ፡

በክልሉ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከልን በማጠናከር የሰላምና የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ ይሰራል - ፖሊስ ኮሚሽን

ሆሳዕና፤ ህዳር 10/2018(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከልን በማጠናከር የሰላምና የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ በበለጠ ሀላፊነት እንደሚሰራ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን "ከጂኦስትራቴጂያዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና" በሚል መሪ ሀሳብ ለፖሊስ አመራሮችና አባላት ለሶስት ቀናት በሆሳዕና ከተማ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን በማልማት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምን በበለጠ ማስጠበቅና ዘላቂ ማድረግ ይገባል፡፡


 

ለዚህም ስኬት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከልን በበለጠ በማጠናከር የሰላምና የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በዚህም የክልሉ ፖሊስ በታማኝነትና በቅንነት ማህበረሰቡን የማገልገል ሀላፊነቱን በበለጠ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።


 

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ሙሰማ ጀማል በበኩላቸው የዞኑ ፖሊስ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም የማስጠበቅና የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዳይስተጓጎሉ ባከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በዞኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናቅቀው የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ፖሊስ ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባር በበለጠ ሀላፊነት ይከናወናል ነው ያሉት፡፡


 

በክልሉ የሰላምና የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ የተሰጣቸውን ሀላፊነት በበለጠ እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ ሳጅን ቤተል ሰጡ ናቸው፡፡

በስልጠናው የክልሉ ፖሊስ፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ ወረዳና ከተማ ፖሊስ አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል፡፡

የስልጠናውን መጠናቀቅ ተከትሎም በሆሳእና ከተማ በመከናወን ላይ ያሉ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች ጉብኝት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም