ነጻ የንግድ ቀጣናው የላኪዎችን ተወዳዳሪነት ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ነጻ የንግድ ቀጣናው የላኪዎችን ተወዳዳሪነት ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡-የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና የጥራጥሬና ቅባት እህሎችን የገበያ መዳረሻ በማስፋት የላኪዎችን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ያስችላል ሲሉ የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ ገለፁ።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን መስከረም 29 ቀን 2018 ምርቶቿን ወደተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመላክ በይፋ መጀመሯ ይታወቃል።
በዚህም ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡና፣ የጥራጥሬ ምርቶችና የቅባት እህሎችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና በየብስ ትራንስፖርት አማካይነት ወደ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ አፍሪካ መላክ ጀምራለች።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለዘርፉ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣናው በአፍሪካ ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ዕድሉ በተለይም የጥራጥሬና የቅባት እህል አምራቾች ምርቶቻቸውን በተሻለ አማራጭ ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን አዲስና ሰፊ ገበያ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ስምምነቱ በአፍሪካ ሀገራት መካከል የተጣሉትን የንግድ ቀረጥና ታሪፎችን ቀስ በቀስ በማስቀረት ለወጪ ንግድ የሚቀርቡ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች በአፍሪካ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የጥራጥሬና ቅባት እህል ላኪ የሆኑት አቶ ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት እና ተወዳዳሪነትን በመጨመር የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን የወጪ ንግድ መጠንና ገቢ ያሳድጋል ብለዋል።
ስምምነቱ ተግባራዊ መደረጉ የአፍሪካን የንግድ ልውውጥ የሚቀይር ነው ያሉት ደግሞ የናይጄሪያ ብሔራዊ የሰሊጥ ዘር ማኅበር ተወካይ እያሱ ይስሃቅ ናቸው።