ቀጥታ፡

የምገባ መርሐ ግብር ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ  ነው 

ጎንደር፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።  

በጎንደር ከተማ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብር በከተማው አየር ጤና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ እንደገለጹት፤ በከተማው የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ  ነው። 


 

ለስኬቱም የከተማ አስተዳደሩ 40 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስፈልግን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ  ባለሀብቶችና ተቋማትን  በማሳተፍ  በማሰባሰብ  ወደ ስራ  መገባቱን ተናግረዋል።     

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ አቶ ሚዛኑ ነቅሎ በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ በ44 ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።   

የምገባ መርሃ ግብሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና የማቋረጥ ምጣኔን በመቀነስ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በትምህርት ዘመኑ ከ1 ሺህ በላይ የቅድመና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ ያሉት ደግሞ የአየር ጤና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሳሙኤል አታላይ ናቸው።


 

ህብረተሰቡ ለምገባ መርሃ ግብሩና ለትምህርት ቤቱ የግብዓት ማሟያ የሚውል ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን  አስረድተዋል።       

ባለፈው ዓመት በትምህርት ቤቱ የተጀመረው የምገባ መርሃ ግብር በተማሪዎች የትምህርት ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።  

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ፤ ወላጆች፤ ተማሪዎችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም