በአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተቻለ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተቻለ
ባሕርዳር/ ደሴ ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሶስት ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የዕፅዋት ጥበቃ ባለሙያ አቶ አበበ አናጋው ፤ የግሪሳ ወፍ በክልሉ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች መከሰቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ቢሮው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከጥቅምት 8/2018 እስከ ሕዳር 6/2018 ዓ.ም ድረስ ባደረገው በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን አስታውቀዋል።
የኬሚካል ርጭቱ ግሪሳ ወፉ በሚያድርባቸው በተለዩ 604 ሄክታር የሚሸፍን ቦታዎች በተካሄደው ርጭት የግሪሳ ወፍ መንጋን ማስወገድ መቻሉን ገልጸዋል።
በርጭቱም 1 ሺህ 208 ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመው፤ በዚህም ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማ ሰብልን ከጉዳት መታደግ መቻሉን ባለሙያው አስረድተዋል።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ደጀኔ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ጅሌ ጥሙጋ እና ደዋጨፋ ወረዳዎች የግሪሳ ወፍ መንጋ ተከስቶ ነበር።
የወፉን ማደሪያ ሥፍራ በመለየት ከ155 ሄክታር መሬት ላይ በተደረገ የአውሮፕላን ኬሚካል ርጭት በሰብል ላይ ጉዳት ሳይደርስ መከላከል መቻሉን ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ በበኩላቸው፤ በቃሉ ወረዳ የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ በአውሮፕላን የታገዘ ኬሚካል ርጭት በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ የደረሰውን ሰብል በወቅቱ ፈጥኖ ከመሰብሰብ ባሻገር ተባይና የግሪሳ ወፍ ሲመለከት ፈጥኖ ለግብርና ባለሙያዎች መረጃ እንዲሰጥ መክረዋል።