የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደመረ አቅም ዜጎችን በማገዝ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደመረ አቅም ዜጎችን በማገዝ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
ወላይታ ሶዶ ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደመረ አቅም ዜጎችን በማገዝና ሃብትን አቀናጅቶ በመምራት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
በወላይታ ሶዶ ከተማ ክልል አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የ2018 ዓ.ም የበጋ ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን በማገዝ ብዙ መሰራቱን አስታውሰዋል።
በተለይም የወጣቶች ወሰን የተሻገረ ነፃ አገልግሎት ሰዎችን ከማገዝም ባለፈ የጋራ ትርክትንና አብሮነትን የሚያጸና ተግባር መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደመረ አቅም ዜጎችን በማገዝና ሃብትን አቀናጅቶ በመምራት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በክረምቱ የተከናወነውን በጎ ተግባር በመሰነቅ ለበጋውም በተሻለ ዝግጅት ዜጎችን ለማገልገል መዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ካሰች ኤልያስ፤ በክልሉ ከ4 ነጥብ 5 ሚልዮን በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በማከናወን ከ8 ነጥብ 3 ሚልዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ከ15 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ዕድሳት፣ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዩኒት ደም መሰብሰቡንና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ይህ መልካም ተግባር በበጋውም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።