የመደመር መንግሥት ከተሞችን የሚመለከታቸው የብልጽግና ማሳያዎችና ማዕከላት አድርጎ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ከተሞችን የሚመለከታቸው የብልጽግና ማሳያዎችና ማዕከላት አድርጎ ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡-የመደመር መንግሥት ከተሞችን የሚመለከታቸው የብልጽግና ማሳያዎችና ማዕከላት አድርጎ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የማጠቃለያ መርሀ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሄዷል።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ታድመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የክትመት ታሪክ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ነው።
ከተሞች የሥልጣኔ ማዕከላት በመሆናቸው የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ከከተሞች ሥልጣኔ ለይቶ ማየት እንደማይቻል ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ከተሞችን በዘላቂ ስትራቴጂ የመምራት፣ በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር እና በኢንዱስትሪያላዊ እሳቤ የገጠር እና ከተማን ትስስር የማሣለጥ ውስንነት እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡
በዚህም የተነሣ የከተሞች ዕድገት ከከተሞች ታሪክ ርዝማኔ ጋር ሊጣጣም አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የመደመር መንግሥት ከተሞችን የሚመለከታቸው የብልጽግና ማሳያዎችና የብልጽግና ማዕከላት አድርጎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በብልጽግና ማሳያነታቸው በከተሞች የሚካሄደው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወደ አነስተኛ መንደሮችና ወደ ገጠር አካባቢዎች ለማስፋፋት እንዲቻል እንደ ሰርቶ ማሳያ እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተሞቹ በራሳቸው የብልጽግና ማዕከላት መሆናቸውን አመልክተው፤ የብዝኃ ዘርፍ ኢንዱስትሪ ማበቢያ ቦታዎች ናቸው ብለዋል።
የከተሞች ፎረም ዋና ዓላማ ከተሞች የብልጽግና ማሳያዎች እና ማዕከላት በመሆን ረገድ የሄዱበትን ርቀት በየሁለት ዓመቱ በአካል እየተገናኙ እንዲገመግሙ እና እርስ በእርስ እንዲማማሩ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪያዊነት ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ የመሪነቱን ሚና የሚጫወቱት ከተሞች መሆናቸውን በማንሳት፤ ለዚህ ደግሞ ግልጽ ርዕይ፣ ዕሳቤ እና ስትራቴጂ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ላይ በመመስረት በሁሉም የልማት መስኮች ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የተጀመረው ከተሞችን ለብልጽግና ጉዞ የማመቻቸት እንቅስቃሴ ዛሬ ወደ አነስተኛ የገጠር ከተሞች እየደረሰ መሆኑን አንስተዋል።
የገጠር ኮሪደር ዋና ዓላማ ገጠሩን በአስተዳደር፣ በመሠረተ ልማትና በክትመት ሥርዓት በማስተሣሠር ወደ ከተማነት ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየሁለት ዓመቱ የሚከበረው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ዝግጅት ዋና ግቡ ከተሞች ለብልጽግና ጉዞ ምን ያህል ተመቻችተዋል? የሚለውን መገምገምና ቀጣዩ ዘመን ካለፈው ዘመን የተሻለ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
10ኛው የከተሞች ፎረም ሲጠናቀቅ በከተሞች ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ አራት ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የመጀመሪያው በከተሞች እያጋጠመ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ማቃለል መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ችግር ለማቃለል የሚያስችሉና የተለያዩ አማራጮችን የያዙ መርሃ ግብሮች ተነድፈው በሁሉም ከተሞች የተለያዩ የቤት መርሃ ግብሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ይሄንን ፕሮግራም የከተማ አመራሮች ቀን ከሌት በመከታተልና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ማሳካት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ሁለተኛው የጽዳትና አረንጓዴ ልማት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ የከተማው ሕዝብ ጽዳትን ባህሉ እንዲያደርግ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሦስተኛው በየአካባቢው የሚገኙ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በአነስተኛ ወጪ፣ የሕዝብን ዐቅም እና ዕውቀት በማዋሐድ፣ የየአካባቢዎቹን ቁሳቁስ በመጠቀም ወደ ቱሪዝም ሀብትነት መቀየር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየአካባቢው ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለኅብረ ብሔራዊ ትስስርና ለወል ትርክት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አራተኛው ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ገብተው እንዲማሩ፣ የአምስት ሚልዮን ኮደርስ ዓይነት መርሃ ግብሮችን እንዲያጠናቅቁ በማድረግ መካከለኛ ባለሙያዎችን በብዛት የመፍጠር ሥራን ማቀላጠፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ መካከለኛ ሙያተኞች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ለመሠማራት እንዲችሉ ሆነው መቀረጽ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
በአጠቃላይ ከተሞች የብልጽግና ተምሳሌቶችና ማዕከላት እንዲሆኑ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ፎረሙ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በተለይም የአፋር ክልል እና የሰመራ ሎጊያ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።