የሽመና ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሽመና ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ነው
ባሕርዳር፤ ሕዳር 10/2018(ኢዜአ)፡ - በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጰያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊ ጋር በማዋሃድ የሽመና ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየን(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።በቴክኖሎጂ ሽግግርና ፈጠራም እንዲሁ።
በተለይም በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቴክስታይል ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የዘርፉን ችግር የሚፈታ ትርጉም ያለውን ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ተማሪዎች ኢንስቲትዩቱ ባቋቋመው ፋብሪካ ውስጥ የንድፈ ሃሳብ ትምህርታቸውን በፋብሪካው ውስጥ በተግባር ልምምድ ታግዘው ብቃት ያላቸው ሆነው እንዲወጡ እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ኢንስቲትዩቱ የዘመናዊ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂን ከሀገር በቀል እውቀት ጋር በማዋሃድ የሽመና ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በፋሽን ዲዛይን እና በፋሽን ቴክኖሎጂ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ተመራቂዎች ፈጥነው የራሳቸውን ድርጅት ከመክፈት ባለፈ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ ሙሐመድ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ኢኒሸቲቭ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን አጠናክሯል።
የኢትዮጵያ ቴክስታይል ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተማሪ-ኢንዱስትሪ፣ ዩኒቨርሲቲ -የኢንዱስትሪ ትስስር በተግባር የተረጋገጠበትና ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለሃገሪቱ የቴክስታይልና ፋሽን ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጭ ተግባራት በተጨባጭ እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጥ ያስቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ በፋሽንና ቴክኖሎጂ ከሀገር በቀል እውቀት ጋር በማዋሀድ የማሕበረሰቡን አለባበስ ትውልዱ እንዲማርበት በሚያስችል መንገድ ዘምኖ መሰራቱ የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ መልካሙ ፀጋዬ ናቸው።
ይህም ወጣቱ ትውልድ ባሕሉን አውቆና ጠብቆ እንዲያድግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ ከቱሪዝም እድገት ጋር ተዋህዶ እንዲቀጥል በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።