በጉጂ ዞን 184 መደበኛ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው ተሻሽሏል - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን 184 መደበኛ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው ተሻሽሏል
አዶላ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የ184 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የመማር ማስተማር ሥራን ውጤታማ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ሳተና ሮባ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት በዞኑ ያሉ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸው ለመማር ማስተማር ስራው እንቅፋት ሆነው እንደነበር አስታውሰዋል።
ችግሩን በህዝብ ተሳትፎ በመፍታት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ በተደረገ የተቀናጀ ጥረትም የ184 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ 29 ሚሊዮን 859 ሺህ ብር የሚገመት የገንዘብ፣ የጉልበትና የአይነት ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም 591 የቅድመ መደበኛ መማሪያ ክፍሎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ውሀ፣ መብራትና መሰል መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ መደረጉን የጠቆሙት ሃላፊው፣ ጠረጴዛና ወንበር ጨምሮ ሌሎች የትምህርት መርጃ ቁሶችም ተሟልተው የመማር ማስተማር ሥራው በተሟላ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የአጥር ዙሪያ፣ የክፍል ውስጥና የግቢ ንጽህና አጠባበቅ ሥራም የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ የማሻሻል ሥራ አንዱ አካል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የአዶላ ከተማ ነዋሪ መምህር ድሪባ ሁንዴሳ ፤ የትምህርት ቤቶቹ ደረጃ መሻሻል የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለመጨመር የራሱ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞችና ህብረተሰቡን በማስተባበር የተከናወኑ የምድረ ግቢ ውበት ሥራዎች የመማር ማስተማር ሥራውን በማጠናከር የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ማገዙን አንስተዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል የትምህርት ጥረትን ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ መምህርት ጸሐይ ጉታ ናቸው።
በመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ላይ መምህራንም ከህዝብና ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡