የወባ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የወባ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዳማ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የወባ ስርጭትን ለመግታትና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጀ አብደና ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለይም የወባ በሽታ ስርጭትን መግታት የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም በምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ በደሌ፣ ኢሉ አባቦር እና ጅማ ዞንን ጨምሮ ስርጭቱ ጎላ ብሎ በሚታይባቸው አካባቢዎች የመከላከል ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በበጀት ዓመቱ አራት ወራትም የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት፣ ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና ጉድጓዶችን የማዳፈን ስራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅና በአጎበር አጠቃቀም ዙሪያ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርት መሰጠቱን ገልጸው ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ መሰራጨቱንም ተናግረዋል።
እንዲሁም ከፍተኛ የወባ ስርጭት በታየባቸው 15 ወረዳዎች የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት ስራው በተለየ መልኩ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ ከተከናወነው የቤት ለቤት ኬሚካል ርጭት ስራ ባሻገር በጎ ፈቃደኞችንና ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተሰራው ስራ ዘንድሮ የተሻለ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
የበሽታውን ስርጭት በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ትብብር የሚጠናከር መሆኑንም አስረድተዋል።