የልማት ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ጉልህ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ጉልህ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡-በመንግሥት ይፋ የተደረጉት ግዙፍ ሀገራዊ ልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የተሻለ በማድረግ ሁሉን አቀፍ እድገት የሚያረጋግጡ ናቸው ሲሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባ ያበሰሯቸው የ30 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ከመሰረተ ልማት ግንባታ በላይ የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መሆናቸው ነው የተመላከተው።
የጉባ ብስራት ከሆኑ ፕሮጀክቶች መካከል የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ ግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣የጋዝ ፋብሪካ፣የነዳጅ ማጣሪያ እንዲሁም ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ቤቶች ግንባታ ይገኙበታል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።
የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አበራ በቀለ፣ኢትዮጵያውያን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም ማሳካት እንደሚችሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
በመንግሥት የተያዙት ትላልቅ ፕሮጀክቶችም የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም የሚያሳድጉ በመሆናቸው እንደ ፓርቲ እንደግፋቸዋለን ብለዋል።
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር)፤ መንግሥት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች ሁሉን አቀፍ ዕድገት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው፤ እንደሀገር እየተተገበሩ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለተግባራዊነቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አበራ በቀለ፣የፕሮጀክቶቹ እውን መሆን የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የተሻለ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ፓርቲዎች መንግስት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ህጋዊ የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋት ይገባል ብለዋል።