አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርዓት የተፈጥሮ ደኖችን ህልውና መጠበቅ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርዓት የተፈጥሮ ደኖችን ህልውና መጠበቅ አስችሏል
ሚዛን አማን፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ተግባራዊ የተደረገው አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርአት የተፈጥሮ ደኖችን ህልውና መጠበቅ ያስቻለ መሆኑን የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ገለጸ።
በኢትዮጵያ ሰፊ የደን ሽፋን ካላቸው አካባቢዎች መካከል የሚጠቀሰው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሁለት በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገቡ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች መገኛ ነው።
የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ለማ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤በክልሉ ከጥንት ጀምሮ ያለው የደን አጠባበቅ ባህል የደን ሃብቶችን መጠበቅ፣ ማልማትና መንከባከብ ያስቻለ እሴት ሆኖ ቀጥሏል።
በዚህም በክልሉ ያለው አጠቃላይ የደን ይዞታ አሁን ላይ ከ760 ሺህ ሔክታር በላይ መሆኑን አንስተው በተለይም በሁለት አካባቢዎች የሚገኙ ደኖች በባዮስፌር ጥብቅ የደን ስፍራነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በካፋና ሸካ ዞኖች የሚገኙ ደኖችን ለመጠበቅ የተቋቋሙ ከ500 በላይ አሳታፊ የደን አስተዳደር ማኅበራት ለደኖቹ ሕልውና መጠበቅ የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አንስተው በቀጣይም የደኖቹን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማሳደግና የኢኮቱሪዝም ቀጣና ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሸካ ዞን የአንድራቻ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሠራዊት ቆጭቶ በበኩላቸው፤ አሳታፊ የደን አስተዳደር ጥበቃ ሥርዓት ከሸካቾ ብሔረሰብ ባህል ጋር የተሳሰረ የሃብት መጠበቂያ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በሥርአቱ ደን ከመጠበቅ ባሻገር ከዘርፉ ኢኮኖሚ በማመንጨት አካባቢውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በወረዳው የዮኪጭጪ ቀበሌ አሳታፊ ደን አስተዳደር ማህበር አባል አቶ ገብረሥላሴ ቶንዶሮ፤ ደንን መጠበቅ ከጥንት የወረስነው ባህል በመሆኑ የትኛውንም የደን ውጤት ያለ ፍቃድና ያለ አግባብ መቁረጥ አይቻልም ብለዋል።
ደኑ በደን ክልልነት ከተመዘገበ በኋላም በአሳታፊ ደን አስተዳደር ተደራጅተው ለደኑ ጥበቃ ከማድረግ ጎን ለጎን በውስጡ ማርን ጨምሮ ኮሮሪማ፣ ጥምዝና ሌሎች የደን ውጤቶችን በማምረት እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል።
የደን ሃብት ጥበቃ የቀደሙት ያወረሱን ሀብታችን በመሆኑ ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን ያለው ደግሞ የዩቲ ቀበሌ የአሳታፊ ደን አስተዳደር ማኅበር አባል ወጣት ተካልኝ ተሰማ ነው።
ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሚቆረጥ ዛፍ እንዳይኖር በአሳታፊ የደን አስተዳደር በወጣው የጥበቃ መርሐ ግብር መሠረት ደኑን እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል።
የአሳታፊ ደን አስተዳደር ማኅበር የአንድ ቀበሌ ነዋሪና በደን አካባቢ ያሉ አባወራ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን በደን ክልል ውስጥ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳይፈጸም በጥበቃ የሚከላከሉበት ሥርአት ነው።
አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርአት ዓላማውም የደን ሀብትን ዘላቂነት ማረጋገጥ፣ የብዝሃ ሕይወትን መጠበቅ፣ የካርበን ክምችትን መጨመር እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦችን ኑሮ ማሻሻል እና ከደን የሚገኘውን ጥቅም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።