ቀጥታ፡

በዓሉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትንና ትስስርን ይበልጥ በሚያጠናክሩ ኹነቶች ይከበራል

ሆሳዕና፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሕብረብሔራዊ አንድነትንና ትስስርን ይበልጥ በሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ኹነቶች እንደሚከበር የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አስታወቀ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቡቶ አኒቶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሕብረብሔራዊ አንድነትንና ትስስርን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

አንዱ የሌላውን ባሕል፣ታሪክና ቋንቋ እንዲያውቅ የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ እንዲጎለብት የበዓሉ መከበር ሚናው ከፍተኛ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡


 

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች በክልሉ ሕዝብ እንግዳ አቀባበል ባሕል መሰረት ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።

በዓሉም ሕብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ኩነቶች እንደሚከበር አስታውቀዋል።

የሀድያ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ እቴነሽ ሙልጌታ በበኩላቸው፥በዞኑ ሆሳዕና ከተማ የሚከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡


 

በዓሉ የአብሮነት እሴቶችን በዘላቂነት በማጠናከር ረገድ ያለውን አስተዋጽኦ መሰረት በማድረግ በሁሉም የዞኑ መዋቅሮች እንዲከበር ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ተግባር ስለመገባቱም ጠቁመዋል፡፡

ከሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ተመስገን ታምሬ በሰጠው አስተያየት፥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የአብሮነት እሴትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግሯል።


 

በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶችን በክብር ተቀብሎ ለማስተናገድ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ዘንድሮ በሆሳዕና ከተማ እንደሚከበር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም