ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚጨበጥና አይቀሬ መሆኑን ያሳየ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በመፍጠርና መፍጠን የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚጨበጥና አይቀሬ መሆኑን ያሳየ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መስሪያ ቤት በዚህ ሳምንት መመረቃቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከእድሜው በላይ የሚጨበጥ ውጤት ማስመዝገብ የቻለ ተቋም ነው፡፡


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በመደመር መንግስት ላይ መፍጠር፣ መፍጠንና በዝላይ ማለፍ የሚሉ ጽንሰ ሀሳቦችን በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የግድ ሁሉንም ሂደት ማለፍ አይጠበቅም ያሉት ኃላፊው፤ ነባራዊውን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ በዝላይ ማለፍ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላትን አቅም መገንባቷን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የታየው የመፍጠን፣ የመፍጠርና በዝላይ የማለፍ ውጤት የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚጨበጥና አይቀሬ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ ያሉ ሥራዎችን ሁሉ ማከናወን የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁሉንም ሥራዎች በፍጥነት፣ በጥራትና በግልጸኝነት ማከናወን እንደሚችል ገልጸው፤ ፈጣን ዕድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በመዲናዋ ሁሉም ተቋማት ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ነዋሪዎች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡትን ቅሬታ መፍታት የሚያስችል አቅም መገንባቱን  ነው የተናገሩት፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት የማያስፈልግበት ቦታ የለም ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ የመዲናዋን ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥና ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፤ የከተማ ሥራ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ሥራ እና ውሳኔ የሚተላለፍበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ከዚህም ባለፈ መረጃዎችን ተንትኖ ለቀጣይ የልማት ዕቅዶች ለማዋል፤ እንዲሁም የከተማዋን የክትመት ሁኔታ ለመቆጣጠር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተከናወኑ አስደናቂ ሥራዎች መዲናዋን በበቂ የክትመት መረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ የሚከናወኑ ህገ ወጥ ግንባታዎችን፣ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴዎችንና ቀጣይ ለመስራት የታቀዱትን በመለየት በቂ መረጃ ይሰጣል ብለዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ  ጀንበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሳለጠ የመንግስት አገልግሎት በመስጠት የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡


 

ከተማ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስጀመሩን ገልጸው፤ በቀጣይ በሌሎችም ዘርፎች በጋራ መስራት እንዳለብን አይተናል ብለዋል፡፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥራዎችን ቀላል ፈጣንና ግልጽ ማድረግ እንደተቻለ በማንሳት፤ ከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን የስማርት ሲቲ ግንባታ ለማላቅ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ ዘላቂና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማጎልበት በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ሥራ ማከናወን ያስችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም