ቀጥታ፡

የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተጀመሩ ስራዎች ውጤት መጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦በጉራጌ ዞን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተጀመሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣት መቻሉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ አስታወቁ።

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ከመላው ሀገሪቷ የተውጣጡ የጋዜጠኞች ቡድን  በጉራጌ ዞን የተካሔዱ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤  ባለፉት ዓመታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸው።                                                                                   

ከእነዚህ መካከል በግብርናው ዘርፍ መስኖ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መቻሉን ነው የጠቀሱት።


 

በሀገር ደረጃ በተጀመረው የሌማት ትሩፋትም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እና በአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉንም አንስተዋል።


 

በመላው ሀገሪቷ በተጀመረው የኮሪደር ልማትም እንዲሁ በገጠርና በከተማ ለኑሮ፣ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ከባቢ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።

የገጠር ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ እንዲቻል በተከናወኑ ተግባራት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመንገድ ግንባታ መከናወኑንም አብራርተዋል።

በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም ጸጋዎችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ለአብነትም በጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ደረጃውን የጠበቀ ሎጅ ለመገንባት እና አካባቢውን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለማልማት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም