ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በብልፅግና ፓርቲ የሥልጠና መድረክ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መነሻ በማድረግ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
በአዳማ በተካሄደው የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ላይ የተሳተፉ የሲዳማ ክልል አመራሮች የጋራ የውይይት መድረክ ዛሬ ማምሻውን ተካሄዷል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በፓርቲው የተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎችን መነሻ በማድረግ በክልሉ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ባጠረ ጊዜ ውስጥ ፍጥነትንና ፈጠራን በማከል ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የበጀት ዓመቱን የሥራ ዕቅድ በመከለስ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።፡
በዚህም በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በከተማ ልማት፣ በግብርናና ገጠር ልማትና በሌሎች የትኩረት መስኮች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የጋራ ተግባቦት መፍጠር እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ገቢራዊ ለማድረግም በክልሉ ያሉ የሰላምና ጸጥታና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎችን በመጠቀም እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠልም የጊዜ፣ የጉልበትና የበጀት ብክነትን በማስቀረት ባጠረ ጊዜ ውስጥ የተነደፉ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡
ሰላምና ልማት ወዳዱን ህዝብ እንዲሁም ባለሀብቱን በማስተባበርም የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በተሻለ ሁኔታ እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
ገቢን አሟጦ በመሰብሰብም የተሻለ የመፈፀም አቅም በመፍጠር ዕቅዶችን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወንም አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል።