ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመጠቀም ባህልን የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘገባዎችን ማጠናከር አለባቸው

አዲስ አበባ፤ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙኃን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመጠቀም ባህልን የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘገባዎች ማጠናከር እንደሚኖርባችው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልማት ሥራዎች የነገዋን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በሚያሳልጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንድትገኝ ያስቻሉ መሆናቸውን የኢዜአ አመራር አባላት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሥራ ኃላፊዎችና የሙያተኞች ቡድን አባላትም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መስሪያ ቤት የቴክኖሎጂ ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ 'ኢንተለጀንስ ለሁሉም' በሚል መሪ ሃሳብ በሁሉም ዘርፍ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ተቋማትም የዕለት ከዕለት ሥራዎቻቸውን በቀላሉ የሚያከናውኑበት ምቹ የቴክኖሎጂ ምኅዳር እየተፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የበርካታ ዓለም ሀገራት የመገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ተቋማት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ጥራትና ፍጥነት ያላቸውን ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ተቋማት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመጠቀም ባህል የሚያሳድጉበትን ግንዛቤ የሚያሳድጉ የዘገባ ስራዎችን መስራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የፈጠራ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም የሙያተኞችን የሥራ ጫና የሚቀንሱበት ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፤ በበኩላቸው በጉብኝቱ ላይ ኢትዮጵያ በዘርፉ በአፍሪካ ከፍ ያለ ስራ ለመስራት ምን እያከናወነች እንዳለች መመልከታቸውን ተናግረዋል።


 

የኢንስቲትዩቱ ጉብኝታቸውም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች መስኮች የኢትዮጵያን የብልጽግና ርዕይ የሚያሳካ ምቹ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን እንደታዘቡም ገልጸዋል።

በኢንስቲትዩቱም ታዳጊዎች የኢትዮጵያን መፃኢ እጣ ፋንታ በተሻለ ጉዞ ማጀብ የሚያስችል የፈጠራ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት ከውጭ የሚገባን ቴክኖሎጂ ብቻ የመጠቀም ባህል በመቀየር ለአህጉሪቷ ጭምር በአርዓያነት የሚጠቀስ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፈጠራ ስራዎች እያከናወነች እንደምትገኝ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።


 

በጉብኝቱ የተሳተፉ የኢዜአ አመራር አባላትም፤ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለአፍሪካዊያን ጭምር ትምህርት የሚሰጥ አመርቂ ስኬት ማስመዝገቧን እንደታዘቡ ገልጸዋል።


 

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የፈጠራ ሙያተኛን ለማፍራት የሚከናወኑ ተግባራትም የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለ ማድረግ በሚያስችል የትልም ጉዞ ላይ መሆኗንም ተናግረዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኅዳር 07/2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃን መርቀው ስራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም