ኢትዮጵያና አዘርባጃን ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይሰራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና አዘርባጃን ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይሰራሉ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና አዘርባጃን የፓርላማ፣ የህዝብ ለህዝብና የኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ የአዘርባጃን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኤልቺን አሚርባዮቭን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ህዝብ ለህዝብ ትስስር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
የሁለቱ ሀገራት ፓርላማዎች ትስስር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር አጋዥ መሆኑ ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለረጅም ዓመታት የዘለቀና እየተጠናከረ የመጣ ነው።
ሁለቱ ሀገራት ሲቪል ሰርቪሱን ለማጠናከር እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓትን ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ የአዘርባጃን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
አፈ ጉባዔው አዘርባጃን ኮፕ 29ን ማስተናገዷን አንስተው ኢትዮጵያ የኮፕ 32ን በውጤታማነት እንድታስተናግድ አዘርባጃን ያላትን ልምድና ተሞክሮ እንድታጋራ ጠይቀዋል።
የአዘርባጃን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኤልቺን አሚርባዮቭ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና አዘርባጃን ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል።
አዘርባጃን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ለዓመታት የዘለቀ ግንኙነት፣ የህዝብ ለህዝብ፣ የባህልና የንግድ ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን ለማስተናገድ በመመረጧ እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት አምባሳደር ኤልቺን፤ አዘርባጃን ኮፕ 32 በስኬት እንዲጠናቀቅ ሀገራቸው ያላትን ልምድና ተሞክሮ ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።