ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፖለቲካ ሴራ አላግባብ ያጣችው የባህር በር በእውነትና በፍትህ ይመለሳል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በፖለቲካ ሴራ ያጣችው የባህር በር በእውነት እና በፍትህ ይመለሳል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳ ገለጹ፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የየካ ክፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ዋና ሰብሳቢ መልዓከ-ኃይል አባ ኃይለገብርኤል ከተማ ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ብለዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችው እድገቷን እንደ ስጋት በሚመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶቿ ሴራ እና በወቅቱ በነበሩ የአገራችን መሪዎች ቸልተኝነት መሆኑንም አንስተዋል።

አገሪቱ የባህር በር ማጣቷ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞቿ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ መቆየቱን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንደነበረች ታሪካዊ ማስረጃዎችን በመጥቀስ፣ የባህር በርን መመለስ የፍትህ ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችው የባህር በር በእውነት ይመለሳል፤ የእውነት ጊዜው ደግሞ አሁን ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ሸሪፍ በበኩላቸው፤ በአሻጥር የሄደውን የባህር በራችንን በሰላም እናስመልሳለን ብለዋል፡፡


 

የአሁኑ ትውልድ የባህር በርን የማስመለስ አደራ እንደተጣለበት በመረዳት ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት በማለት አስገንዝበዋል፡፡

አሰብ የኛ የኢትዮጵያውያን ናት፤ በመሆኑም እኛ የሃይማኖት አባቶች በማስመለስ ሒደቱ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ኢኮኖሚያያዊና ማህበራዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ያነሱት ደግሞ አባ ገዳ ወልደአብ ገብረአብ ናቸው፡፡


 

እነዚህ ለውጦች የተመዘገቡት መንግስትና ህዝብ በጋራ መስራት በመቻላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ የባህር በር ለማስመለስ በሚደረገው እንቅስቃሴም እንደ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንቆማለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም