በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዩጋንዳ ድል ሲቀናት ሶማሊያ እና ኬንያ አቻ ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዩጋንዳ ድል ሲቀናት ሶማሊያ እና ኬንያ አቻ ተለያዩ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ እየተደረጉ ይገኛል።
በምድብ አንድ በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ ዩጋንዳ ሱዳንን 9 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።
ኦውን ሙኪሳ እና ኤዜ ኮምቢ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ቶማስ ኦጌማ፣ ኦዊኖ ጆን በብሪያን፣ ኢስማኤል ፋሃድ፣ ባቢ አብዱልሻኩር እና አርንሎድ ካዬምባ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ዩጋንዳ በስድስት ነጥብ ምድቡን መምራት ጀምራለች።
በአንጻሩ ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ሱዳን ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃን ይዛለች።
የዩጋንዳው ኦውን ሙኪሳ በውድድሩ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ወደ አራት ከፍ በማድረግ የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን ተመሳሳይ ግቦች ካለው ኢትዮጵያዊው ዳዊት ካሳው ጋር በጋራ እየመሩ ነው።
በተያያዘም በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተካሄደ የምድብ አንድ ጨዋታ ሶማሊያ እና ኬንያ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
አናስ መሐመድ ለሶማሊያ፣ ራይስ ኦቺዬንግ ለኬንያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በዚሁ ምድብ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳንን 4 ለ 1 በማሸነፍ በስድስት ነጥብ መሪነቷን አጠናክራለች።
በምድብ ሁለት ታንዛንያ ከጅቡቲ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።