በፍትሕ ዘርፉ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በፍትሕ ዘርፉ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አስችለዋል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በፍትሕ ዘርፉ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ምቹና ቀልጣፋ የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ማስቻላቸውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ገለጹ።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በአገር ደረጃ የፍትሕ ዘርፉን አሠራር ለማሻሻል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።
በፍትሕ ሥርዓቱ የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክቶች ተብለው የተለዩ ከአሥር በላይ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቶቹ በሁሉም ክልሎች እየተተገበሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በወሰዳቸው እርምጃዎች ሰፋፊ የትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነፃ የሆነ ዳኝነት ለመስጠት ምቹ መደላደል የሚፈጥሩ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የክልሉን ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ፣ ጥራት ባለው እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
በተለይም የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት ለማረጋገጥ ምቹ የሥራ ቦታዎችንና ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ለማድረግ ዜጎች ባሉበት አካባቢ ሆነው አቤቱታ እንዲያቀርቡ፣ ፋይል እንዲከፍቱ እንዲሁም ለመከራከር የሚችሉባቸው የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት በተጨማሪ ዜጎች አማራጭ የክርክር መፍቻ ሥርዓቶችን እንዲጠቀሙ ለማበረታታት በክልሉ የባህል ፍርድ ቤቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የዳኞችን አቅም የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም የክልሉን የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት እንደገና የማደራጀት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።
የዳኝነት ሥርዓቱን ግልጽ፣ ተጠያቂ፣ ምቹና ተደራሽ ለማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ማገዝ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ሀገር ከደረስንበት የዕድገት ደረጃ አኳያ ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በተለይም ለፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ዳኝነት ለመስጠት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በፍትሕ ዘርፉ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ ወሳኝ መሆናቸውን አንስተው፤ የተገልጋዮችን እንግልት ከማስቀረት አኳያ ውጤት ማስገኘታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የዳኝነት አገልግሎቱን ይበልጥ ግልጽና ተጠያቂ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል።