በአማራ ክልል አራት የገቢ ግብር አዋጆች ላይ ማሻሻያ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል አራት የገቢ ግብር አዋጆች ላይ ማሻሻያ ተደረገ
ባሕርዳር፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል በቴክኖሎጂ ታግዞ ዘመኑን የሚመጥን ግልጽና ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ አራት አዋጆች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ተገለጸ።
በአዋጆቹ ዙሪያ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ አማረ ሰጤ በመድረኩ ላይ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የታክስ መሰረትን ለማስፋት፣ ፍትሃዊነትንና ገልፅነትን ለማረጋገጥ አዋጆችን ማሻሻል አስፈልጓል።
የተሻሻሉትም የክልሉ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ፣ የግብርና ስራዎችን ግብር ለመወሰን፣ የመንግስት ገቢ ቴምብር ቀረጥ ክፍያ እና የኤክስይዝ ታክስን ጨምሮ አራት አዋጆች መሆናቸውን አንስተዋል።
የአዋጆቹ መሻሻልም የሕዝብን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ለማስፋትና ፍትሃዊነትን ያረጋገጠ የታክስ ስርዓት አስተዳደር ለመዘርጋት እንደሚረዳ ገልጸዋል።
የተሻሻሉት አዋጆች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የቆዩትን በመተካት አሁን ላይ ወቅታዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችንና አዳዲስ የገቢ አማራጮችን ለማስፋት በሚያስችል መንገድ የተዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል።
አዋጆቹ ከባለድርሻ አካላት የሚነሱ የግብአት ሃሳቦችን በማካተት በቅርቡ በሚካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ የሚጸድቁ ይሆናል ብለዋል።
አዋጆቹ መሻሻላቸው በቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመኑን የሚመጥን የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ተግባራዊ የማድረግ ሂደትን የበለጠ የሚያፋጥን ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ናቸው።
እነዚህም የክልሉን የ25 ዓመት አሻጋሪ የእድገትና የዘላቂ ልማት ዕቅድ በአግባቡ ለመፈጸም የሚያስችሉና ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰላሙ ደረጀ በበኩላቸው፤ አዋጆቹ አዳዲስ የፌዴራል ተሞክሮዎችን በማካተት ፍትሃዊ የግብር አስተዳደር ስርዓትን ለመተግበር እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ አርሶ አደሮችና የህግ ምሁራን ተሳትፈዋል።