ቀጥታ፡

በክልሉ የተሟላ እውቀትና ስብዕና ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል

ቦንጋ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትምህርት ሥራን ውጤታማነት በማረጋገጥ የተሟላ እውቀትና ስብዕና ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ።  

በቦንጋ ከተማ አስተዳደር የተገነባው ሸታ ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል።


 

በምረቃው ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊና የመማር ማስተማር ዘርፍ ሀላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ የትምህርት ስራን ውጤታማነት በማረጋገጥ ብቁ ዜጋ ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።


 

የትምህርት ጥራትን ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ በማስጠበቅ ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ ተገቢውን እውቀትና ክህሎት እንዲይዙ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።

ለዚህም ደረጃቸውን የጠበቁና ግብአት በበቂ ሁኔታ የተሟላላቸው 61 ሞዴል ቅደመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ቀድመው የተጠናቀቁት 26ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፤ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ የሚሰሩ ሥራዎች ውጤታማ ሆነው እንዲቀጥሉ ለትምህርት ጥራት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ገልጸዋል።


 

ታዳጊ ልጆች መልካም ስነምግባርና ተገቢ እውቀት ጨብጠው እንዲያድጉ በዞኑ 17 ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ  መሆኑን ገልፀዋል።

ህፃናት ከታች ጀምሮ በጥሩ ስነምግባርና በእውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተክለአብ ቡሎ (ዶ/ር) ናቸው። 


 

ከዚህ ቀደም የነበረው መማሪያ ክፍል ለሕጻናቱም ሆነ ለመምህራን ምቹ አልነበርም ያሉት መምህርት አበባ ገብሬ ፣ ዛሬ የተመረቀው ትምህርት ቤት ችግሩን ከመፍታት ባለፈ የሥራ ተነሳሽነትን ያሳድጋል ብለዋል።


 

በአካባቢያቸው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት መገንባቱ እሳቸውን ጨምሮ ልጁን በግል ትምህርት ቤት ከፍሎ ማስተማር ለማይችል ወላጅ ትልቅ እፎይታ መሆኑን የገለፁት ደግሞ አቶ መላኩ ማሞ የተባሉ የተማሪ ወላጅ ናቸው።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም