የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአርሶ አደሮችን የደረሱ ሰብሎች ሰበሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአርሶ አደሮችን የደረሱ ሰብሎች ሰበሰቡ
አክሱም፤ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የትምህርት ማህበረሰቡ የአርሶ አደሮችን የደረሱ ሰብሎች ሰበሰቡ።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር በርህ ታፈረ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ስራ በተጓዳኝ በማህበረሰብ አገልግሎት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በመኸሩ የለማው የአርሶ አደሮች አዝመራ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ተማሪዎችና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ በዘመቻ የስብሰባ ስራ አከናውነዋል ብለዋል።
በዘመቻውም ከህዳር 07 እስከ ህዳር 09/2018 ዓ.ም በላዓላይና ታሕታይ ማይጨው ወረዳዎች የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
በምርት መሰብሰብ ዘመቻውም በአካልና ጉዳተኞችና በአቅመ ደካማ ወገኖች ማሳ ላይ የደረሰ የሰብል ምርት መሰብሰቡን ገልፀው፤ ዩኒቨርሲቲው በዘመቻው ላይ ለተሳተፉ የከተማ ነዋሪዎችም ነፃ የመጓጓዣ አገልግሎት ማቅረቡን አብራርተዋል።
ምርት ከተሰበሰበላቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አባዲት ገብረስላሴ እና አርሶ አደር አክሊሉ ፍስሃ ፅዮን፤ የደረሰ ሰብላቸው በነፃ የተሰበሰበላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ምርቱ ለብልሽት እንዳይዳረግ ከመሰብሰቡ ባሻገር ለጉልበት ሰራተኞች ያወጡት የነበረውን ወጪ ያስቀረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በሰብል መሰብሰብ ዘመቻው ላይ የተገኘው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ተማሪ ቴዎድሮስ ለአረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካማ ወገኖችን ነፃ አገልግሎት በመስጠታችን ተደስተናል ብሏል።
በቀጣይም በሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲልም አረጋግጧል።