ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት ማሽን ስራ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት ማሽን ስራ አስጀመረ
ነቀምቴ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ሪፈራል ሆስፒታል ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ በድጋፍ ያገኘውን የኩላሊት እጥበት ማሽን ስራ አስጀመረ።
ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው የተገለጸው የኩላሊት እጥበት ማሽኑ በዋናነት በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ የሚገኙ ታካሚዎችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በለጠ እንዳሉት ማሽኑ በቀን ለአስራ ሁለት ሰው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው።
ዛሬ ስራ የጀመረው ማሽን የታካሚውን እንግልት እና ወጪ የሚቀንስ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና የኩላሊት ሰብስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ካሳሁን በንቲ፣ በድጋፍ የተገኘው የህክምና ማሽን የሆስፒታሉ ታካሚዎች ፈጣን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እድልን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት አባገዳ አስፋው ከበደ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ በአዳዲስ የህክምና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቱ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
የኩላሊት በሽታ የበርካታ ወገኖች የጤና ስጋት በመሆኑ ሆስፒታሉ ለህክምናው የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ሼህ ተማም መሀመድ ናቸው።
ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መታከም ለብዙ ወጪ እና እንግልት ይዳርጋል ያሉት ሼህ ተማም ይህ የህክምና አገልግሎት በነቀምቴ ከተማ መጀመሩ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ መሆኑን አንስተዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቨ ሪፈራል ሆስፒታል አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።