ቀጥታ፡

ከስድስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በኩታ-ገጠም እርሻ ገበያ ተኮር ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ ይሆናሉ 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ሁለተኛው ምዕራፍ የኩታ-ገጠም እርሻ ፕሮግራም ከስድስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ገበያ ተኮር ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

ሁለተኛው የኩታ-ገጠም እርሻ ፕሮግራም ዛሬ ይፋ ሆኗል።

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በዚሁ ጊዜ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ለማዘመንና የአርሶ አደሮችን ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኩታ-ገጠም አስተራረስ ዘዴ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የኩታ-ገጠም እርሻ ፕሮግራም በአነስተኛ ማሳ በተበታተነ መንገድ የግብርና ስራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩ ከአራት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን አንስተዋል።

የኩታ ገጠም እርሻ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ  ምርቱን ለገበያ እንዲያቀርብ ማስቻሉንም አንስተዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የኩታ ገጠም እርሻ ፕሮግራም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ግብርናውን የሚያዘምኑ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።

በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፣ በምርቶች ላይ እሴት መጨመር እንዲሁም የገበያ ሰንሰለቱን ማሳጠር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በፕሮግራሙ አርሶ አደሮች ከማምረት ባለፈ ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩበት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያገኛሉ ብለዋል።


 

አርሶ አደሩ በክላስተር በመደራጀት ገበያ ተኮር ምርቶችን በብዛትና በጥራት እንዲያመርትና ምርቶቹን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ ህጋዊ አሰራር የሚዘረጋ መሆኑንም ነው ያብራሩት። 

በመጀመሪያው ፕሮግራም ሰብል ላይ ብቻ ትኩረት መደረጉን አስታውሰው፣ሁለተኛው ምዕራፍ ከሰብል ባለፈ በተመረጡ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና፣ በእንሰት እንዲሁም በእንሰሳት እርባታ ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱኑ ክሮግስትሮፕ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኩታ ገጠም እርሻ በርካታ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሏን አድንቀዋል።

ዴንማርክ ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ትደግፋለች ብለዋል።

ሀገራቸው ለሁለተኛው ምዕራፍ የኩታ ገጠም እርሻ ፕሮግራም የ79 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም