መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ተግባራት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ተግባራት እያከናወነ ነው
ሮቤ፤ ሕዳር 9 /2018 (ኢዜአ)፡- መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሀነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) አስታወቁ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሀነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) ከሻሸመኔ ካምፓስ መምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች ጋር በትምህርት አሰጣጥ ሂደት ላይ ከተወያዩ በኋላ እየተከናወነ የሚገኙ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራዎችን ተመልክተዋል።
ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው መንግስት በትምህርት ዘርፍ ያጋጠመውን የጥራት ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው።
መንግስት ችግሩን ለመሻገር የሚያስችሉ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ገልፀው የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችንም እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።
የትምህርት ሥርዓቱን የማሻሻል ስራዎች፣ የፈተና ሥርዓቱን የመቀየር ሂደት በአገር ደረጃ እየተደረጉ ከሚገኙ የጥረቱ ማሳያዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ይህንኑ መነሻ በማድረግ የራሱ መምህራን ችግሩን ከመረዳት ባለፈ ከችግሩ መውጫ መንገዶቹ ላይ ምርምር እንዲያካሄዱና ምክረ ሀሳብ እንዲለግሱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ተግባር በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምር ፕሮጀክቶችን በማከናወን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ ናቸው።
ከመምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች ጋር በተደረገው ውይይት ለትምህርት ጥራቱ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።
በሻሸመኔ ካምፓስ ከሚገኙ መምህራን፤ ሠራተኞቹና ተማሪዎች ጋር የተደረገው የውይይት መድረክም ይህንኑ ዓላማ ያደረገና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት እንዲቻል ታስቦ መዘጋጀቱን አክለዋል።
መንግሥት በትምህርት ጥራት ላይ ያጋጠመውን ስብራት ለመጠገን ለጀመራቸው ተግባራት ስኬታማነት ሙያዊ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ መምህር ያስን ዲማ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኛ የሆኑት አቶ ዳኒኤል ዩሀንስ በበኩላቸው እንዳሉት ቀደም ባሉት ዓመታት የትምህርት ተደራሽነት ከማሳደግ አንጻር የተሰራው ስራ በጥራት ላይ ለመድገም በመንግሥት እየተሰሩ የሚገኙ ጥረቶች አበረታች ናቸው።
መንግስት የጀመራቸውን የትምህርት ጥራት ላይ ያተኮሩ ተግባራት ስኬታማ ለማድረግ ሙያዊ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በመማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ያተኮሩ ሀሳቦችና የወደፊት አቅጣጫዎች በማስቀመጥ የተሻለ ሥራ ለመስራት ከመግባባት ተደርሷል ነው የተባለው።