ቀጥታ፡

የአፍሪካን ዘላቂ ብልጽግና ለማረጋገጥ ለክህሎትና ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦የአፍሪካን ዘላቂ ብልጽግና ለማረጋገጥ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለክህሎትና ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የግሉ ዘርፍ ልማት፣ ቀጣናዊ ውህደት፣ ንግድ፣ የመሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ኮሚቴ አራተኛው ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል፡፡  

መደበኛ ስብሰባው "ለዘላቂ እና አሳታፊ ዕድገት ቀጣናዊ ውህደትን ለማሳደግ የዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ፈጠራን መጠቀም" በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል፡፡

በውይይቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራ የአፍሪካን ቀጣናዊ ትስስርና ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡


 

የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክላቨር ጋቴቴ ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ በአህጉራዊ ውህደትና በፈጠራ ላይ በመመስረት ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ወደ ዕድል መለወጥ ይገባታል ብለዋል፡፡ 

ዓለም በፈጣን የቴክኖሎጂ ዑደት፣ የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል፡፡

አፍሪካ በርካታ ታዳሽ ኃይሎች ያሏት መሆኑን የገለጹ ሲሆን በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገችውን የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ጨምሮ ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ሃብቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አፍሪካ ፈጠራን በመጠቀም የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እና መድኃኒት የሚያደርሱ ድሮኖችን በመስራት ለፈተናዎቿ ምላሽ መስጠት መጀመሯን በበጎ አንስተዋል፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርታማነትን በዓመት እስከ 40 በመቶ ሊያሳድግ እንደሚችል ጠቅሰው፤ አፍሪካ ይህን ማስፋፋት ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡ 


 

በአፍሪካ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ድንበር ተሻጋሪ የሆነ የዲጂታል ቴክኖሎጂ  መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአባል ሀገራትና ከአጋሮች ጋር በመተባበር የበለጸገች አፍሪካ ለመገንባት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ ልማት፣ ቀጣናዊ ውህደት፣ ንግድ፣ የመሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ማማድጃም ዲኒስ ድጃሎ በበኩላቸው፤ አፍሪካ ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ምርታማነትን ማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ፣ በክህሎትና በፈጠራ ላይ ማተኮር አለባት ብለዋል፡፡ 


 

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እሴትን የሚጨምሩና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ በመሆናቸው በስፋት መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገትና ብልጽግና ምርታማነትን በፈጠራ ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም