ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን ለማሳካት የአመራር ብቃትን ማሳደግ አለባቸው

ደሴ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፡- ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን ለማሳካት ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት የአመራር ብቃትን ማሳደግ እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመሪነት ብቃትን ለማጎልበት የሚያስችሉ 10 ሰነዶችን በማዘጋጀት ቀጣይነት ያለው የስልጠና መርሃ ግብርን ዛሬ አስጀምሯል።


 

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተቋማት አደረጃጀትና አመራር ዴስክ ኃላፊ አቶ ጫኔ አደፍርስ እንደገለጹት፤  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን ለማሳካት የአመራር ብቃትን ማሳደግ አለባቸው።

የአመራር ብቃትን በማሳደግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አውስተዋል።


 

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሰነዶችን በማዘጋጀት ዛሬ ያስጀመረው የአመራር ስልጠና የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለማስወገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም ከዘልማድ አሰራር በመውጣት ዘመኑ የሚጠይቀውን ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት አመራር በመስጠት በዩኒቨርሲቲዎችና የመንግስት መዋቅሮች የሚስተዋሉ  ውስንነቶችን ለማስተካከል እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የመሪና ተመሪ ተግባር  ከብልሹ አሰራር የጸዳ፣ ፈጣን፣ ግልጽና ፍትሃዊ በማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያደርግና ተሞክሮውም ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰፋም አስረድተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤  ዩኒቨርሲቲው በተግባር ተኮር ትምህርት ብቁ፣ ተወዳዳሪና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በዚህም የስልጠና መመሪያ  በማዘጋጀት ጥበብና ብቃት ያለው አመራር በየደረጃው በማፍራት  የመልካም አስተዳደርና የመፈጸም ብቃት ማነስን ችግር ለመፍታት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። 

በአመራር ስልጠናውም የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የቡድን መሪዎች መሳተፋቸውን ጠቁመው፤  በቀጣይ ለዞንና ለከተማ አስተዳደር አመራሮች ለመስጠት ታቅዷል ብለዋል።

የተጀመረው የአመራር ስልጠና ዘርፋችንን በእውቀትና በጥበብ መርተን ውጤታማ ተግባር ለመከወን የሚያግዝ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ልማት ትምህርት ክፍል ዲን ወይንሸት ውቤ ናቸው።


 

ከዚህ ቀደም ልምድ ያላቸው አመራሮችን በመጠየቅና መጽሃፍትን በማንበብ ለመምራት ጥረት ማድረጋቸውን አንስተው፤  በስልጠናው ሳይንሳዊ አመራር በመስጠት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አሳምን አያሌው (ዶ/ር) ፤  ስልጠናው የምንመራውን የስራ ክፍልና የሰው ኃይል ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም