ቀጥታ፡

ፖሊዮን ከኢትዮጵያ በማጥፋት ጤናማ ትውልድ ለማፍራት በቅንጅት እየተሰራ ነው 

ድሬዳዋ ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታን ከኢትዮጵያ በማጥፋት ጤናማ ትውልድ ለማፍራት በቅንጅትና በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

 "የልጅነት ልምሻን እናጥፋ፤ ያልተከተቡ እና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ልጆችን በሁሉም የክትባት አይነት ማድረስ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ የዓለም የፖሊዮ ቀን በድሬዳዋ በውይይት ተከብሯል።  


 

ቀኑን ምክንያት በማድረግም በፖሊዮ ዘመቻ ወቅት ያልተከተቡ ህፃናትም ክትባት አግኝተዋል።

በሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ ዶክተር ሴና ዱጋሳ ፤ ህፃናትን በሁሉም የክትባት አይነቶች ተደራሽ በማድረግ ጤናማ ትውልድ የማፍራቱ ተግባር  ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1988 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖሊዮን ጨርሶ በማጥፋት ንቅናቄ ውስጥ የተወጠኑትን በቁርጠኝነት በመተግበር ለሕፃናት ጤና መሻሻል ወሳኝ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ተናግረዋል። 

መደበኛ ክትባትን በማጠናከር፣ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎችን በማካሄድ፣ የፖሊዮ በሽታ ቅኝት በማድረግ እና በድንበር አካባቢ ከሚገኙ አጎራባች ሀገራት ጋር በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል። 

በተከናወኑ ተግባራት ፖሊዮ የሚያስከትለውን ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ መቻሉን ጠቅሰው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ህጻናትን ከሕመም፣ ከሞትና አካል ጉዳተኝነት ለመታደግ መቻሉን አስረድተዋል። 

ፖሊዮን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት በቀጣይ መደበኛ የክትባት ሽፋን ዝቅ ባለባቸው አካባቢዎች ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ የመከላከል ሥራው በቅንጅትና በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል። 

ዛሬ በድሬዳዋ የተከበረው የዓለም የፖሊዮ ቀን ከዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚሰሩ ሥራዎችን ለማጠናከር እንደሚያግዝም ነው ዶክተር ሴና የገለጹት።

በሽታ መከላከል ማዕከል ያደረገው አገር አቀፍ የጤና ፖሊሲ በአስተዳደሩ በቁርጠኝነት መተግበሩ የህፃናት እና የእናቶች ጤና በከፍተኛ ደረጃ እንዲሻሻል አድርጓል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው። 


 

ድሬዳዋ ካላት የመልካምድር አቀማመጥ አንፃር ለፖሊዮ በሽታ ተጋላጭ በመሆኗ ይህን ያማከለና በገጠርና በከተማ ባሉ ሁሉም ጤና ተቋማት ክትባቱን ለህፃናት ተደራሽ በማድረግ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች ፖሊዮ እንዳይከሰት መከላከል መቻሉን ገልፀው የተገኙትን ውጤቶች በማላቅ ፖሊዮን ለማጥፋት አስተዳደሩ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል። 


 

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ የበሽታ መከላከል ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ማሊሞ ሳሪ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የፖሊዮ በሽታን ለማጥፋት እያከናወነችው ያለውን ውጤታማ ስራ ይበልጥ ለማሳደግ በትብብር የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 

ቀኑን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ የኃይማኖት አባቶች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ አመራሮች እና ባለድርሻዎች የፖሊዮ በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የሚከናወኑ ሥራዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ተግተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም