ቀጥታ፡

የሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እያደገ መጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ያለው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሁለተኛው የኢትዮ-ሳዑዲ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በዚሁ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) ፤ የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው በተለይ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ምርጫቸው ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ  ማደግ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ስጋን ጨምሮ በርካታ የግብርና ምርቶችን የምትልክ ሲሆን በአንፃሩ ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን ከሳዑዲ እንደምታስገባ ተናግረዋል።

የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ማዕድንን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች ኢንቨስት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ሪፎርሙ ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል፡፡


 

በአሁኑ ወቅት የበርካታ ሀገራት ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ እያደረጉ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡ 

ይህ ደግሞ ለሀገር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እና ለስራ እድል ፈጠራ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ሳሊህ አልሞግቢል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ምርጫቸው እያደረጓት መምጣታቸውን ተናግረዋል።


 

ሀገሪቱ ተግባራዊ ያደረገቻቸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎች ለባለሃብቶች ምቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በፎረሙ የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የሁለቱ አገራት ባለሃብቶች  ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም