በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳንን አሸነፈች - ኢዜአ አማርኛ
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳንን አሸነፈች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የምድብ አንድ ጨዋታ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳንን 4 ለ 1 አሸንፋለች።
በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ዳዊት ካሳው ሶስቱን ግቦች በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።
ዳዊት በውድድሩ ላይ ሀትሪክ የሰራ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። እንየው ስለሺ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ፓኖም ጁዎ ለደቡብ ሱዳን ብቸኛውን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በተጋጣሚው ላይ ከፍተኛ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ነጥቧን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ የምድቡን መሪነት አጠናክሯል።
ቡድኑ ቀጣይ ጨዋታውን አርብ ህዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ከሶማሊያ ጋር ያደርጋል።
ደቡብ ሱዳን በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃ ይዛለች።
አጥቂው ዳዊት ካሳው በውድድሩ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ አራት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል።
በምድብ አንድ ሌላኛው መርሃ ግብር ሶማሊያ ከኬንያ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።