ቀጥታ፡

ሪፎርሙ የሀገረ መንግሥት ግንባታ አጀንዳ ማሳኪያ መሳሪያ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን በመፍጠር የሀገረ መንግሥት ግንባታ አጀንዳ ማሳኪያ መሳሪያ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ከፈጠረች ከመቶ ዓመታት በላይ ብትሻገርም የዜጎችን ፍትሐዊና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት የማግኘት ፍላጎት ማርካት አልቻለችም፡፡

በዚህም በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት አገልግሎት ሪፎርም ተደርጎ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬት ከዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሳያመጣ ቆይቷል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ለተቋማት ግልጽ ተልዕኮ የሰጠ ነው፡፡

ሪፎርሙ የዜጎችን የመንግሥት አገልግሎት ፍላጎት በማርካት ዘመን ተሻጋሪ ተቋማት የመፍጠርና የሀገረ መንግስት ግንባታ ተልዕኮን ማሳኪያ መሳሪያ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስታውሰው፤ ይሄኛው በስፋት፣ በጥልቀትና ግልጽ ተልዕኮ የተሰጠው መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ኢትዮጵያን የማሻጋር ትልም ስኬት ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት መታገዝ እንደሚገባ ጠቅሰው፤  ሪፎርሙ የአደረጃጀት፣ አሰራርና የቴክኖሎጂ ውስንነቶችን ያርማል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፃፏቸው መፅሃፎች ላይ ዘላቂ ተቋማትን መገንባት ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፤ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን ዕዳን ወደ ምንዳ የመቀየር ግብ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታዋን አላጠናቀቀችም ያሉት ሚኒስትሯ፤ ዘመናዊ ተቋማትን ለመገንባት የህግ፣ አሰራርና ሥርዓት መሻሻያ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በፈጠራና በፍጥነት በመስራት የኢንተርፕረነርሺፕ ተቋማትን በመፍጠር ሂደት ላይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በሪፎርሙ የተቀመጡ ምሰሶዎችን ገቢራዊ በማድረግ የሰው ሀይላችንን የመፈጸም አቅም አሳድገናል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ለሀገራዊ ተልዕኮው የጎላ አበርክቶ እያደረገ መሆኑን በማንሳት፤ ቀልጣፋና ግልጽ አገልግሎት በመስጠት ለሌሎች ልምድ ማካፈል የሚያስችል አቅም መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

ሰራተኞችን በማሳተፍ የተቋሙን ችግር የሚፈቱና ተልዕኮዎቹን ለማሳካት የሚያስችሉ ሀሳቦች ያለማቋረጥ የሚመነጩበት ተቋም ሆኗል ብለዋል፡፡ 

የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርሙ ከራሳችን ልጆችና ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ማሰብ፣ መንደፍ፣ መተግበርና ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያውያን የለማውን የኢትዮጵያ ገበያ መረጃ ሥርዓት ከስምንት በላይ የአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ ለማድረግ መጠየቃቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ይህ የኢትዮጵያን መቻለ ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሺፕ ፕሮግራም ከበርካታ ተቋማት የስልጠና ጥያቄዎች እየቀረበለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም