ቀጥታ፡

ዩኒቨርስቲውን ወደ ራስ ገዝነት የሚያሸጋግሩ የዝግጅት ተግባራት እየተጠናቀቁ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ወደ ራስ ገዝነት የሚያሸጋግሩ የዝግጅት ተግባራት እየተጠናቀቁ መሆኑን የዩንቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።     

ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) የዩንቨርሲቲውን 75ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ በዓልና ወደራስ ገዝነት ለመሸጋገር እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።    

በመግለጫቸውም ዩኒቨርሲቲውን ወደራስ ገዝነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን አንስተዋል።      

ዩንቨርሲቲው እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር ከ2024 እስከ 2028 በአምስት ዓመታት የሚተገብረው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ መተግበር መጀመሩን ለአብነት ጠቅሰዋል።  

ዓለምአቀፋዊነት እና አጋርነት፣የኃብት ማፈላለጊያና ምንጭ ማስፊያ፣የተማሪዎች ቅበላ እንዲሁም የምርምርና ኢኖቬሽን ፖሊሲዎች ጸድቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም አብራርተዋል።   

ዩንቨርሲቲው የሚሰጣቸው ፕሮግራሞች ላይ ግምገማ በማድረግ ፕሮግራሞች እንዲሸጋሸጉ መደረጉን ጠቁመው ከ500 በላይ የነበሩ የአካዳሚክ ፕሮግራሞችን ወደ 418 እንዲሸጋሸጉ መደረጉን ተናግረዋል። 

ዩንቨርሲቲው በሥሩ ያሉ የምርምር ኢኒስቲትዩቶችና ኮሌጆችንም የማሸጋሸግና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የአሰራር ማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዱንም አስረድተዋል።  

በዩንቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኛውን ምዘና በማድረግ የመመደብ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ያሉት ሳሙኤል (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲውን ወደ ራስገዝነት ለማሸጋገር የተጀመሩ ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል።

የዩንቨርስቲው የቀድሞ የሴኔት ሕግን ከራስ ገዝነት ማቋቋሚያ አዋጅ እና ደንብ ጋር በተጣጣመ መልኩ የማውጣት ተግባራት መከናወኑን ጠቁመው በአዲስ መልክ የተዘጋጀው የሴኔት ሕግ ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር አጣምሮ የያዘ መሆኑን አስረድተዋል።        

እንደ ሳሙኤል(ዶ/ር) ገለጻ ዩንቨርሲቲው ባለፉት 75 ዓመታት የተማረ የኃው ኃይል በማፍራት፣በጥናትና ምርምር እና ሌሎችም ዘርፎች ያበረከተውን አስተዋጽኦ ለመዘከር የአልማዝ እዮቤልዩ በዓል ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።    

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የበጎ ፈቃድ ሳምንት መርሃ ግብር እንደሚካሄድ አመልክተው የፓናል ውይይቶችና ስፖርታዊ ውድድሮችን ጨምሮ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ታህሳስ 1943 ዓ.ም የተመሰረተው አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ 50 ተማሪዎችን በማስተማር ሥራውን የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ170 በላይ ሙሉ ፕሮፌሰሮች፣ከ10 ሺህ በላይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም መፍጠሩን ከዩንቨርስቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በጥቁር አምበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኩልም በየዓመቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ህክምናና  እንክብካቤ እንደሚያገኙም የዩንቨርሲቲው መረጃ ያመለክታል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም