ቀጥታ፡

የማሾ ሰብልን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ሰቆጣ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፡- የማሾ ሰብልን ምርታማነት ለማሳደግ በስብጥር በመዝራት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ22 ሺህ ኩንታል በላይ የማሾ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑም ተመላክቷል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ለገበያ እየቀረበ ያለው ምርት በመኸር ወቅት ለምቶ የተሰበሰበ ነው።  


 

የማሾ ምርት ለወጪ ንግድ ባለው ተፈላጊነትና በምርታማነቱ በአርሶ አደሩ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የማሾ ልማትን ለማስፋፋት በተሰራው ሥራም ባለፈው የመኸር ወቅት 3ሺህ 249 ሄክታር መሬት በማሾ እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል።

ከለማው መሬትም ከ22 ሺህ ኩንታል በላይ የማሾ ምርት መሰብሰቡንና በአሁኑ ወቅትም ምርቱ ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የማሾ ሰብል ከሌሎች የሰብል አይነቶች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ምርት መስጠቱ፣ ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚ መሆኑና በገበያ ያለው ተፈላጊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአርሶ አደሩ ያለው ተቀባይነት እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

በዚህም በአስተዳደሩ ቆላማ በሆኑት ዝቋላ፣ ሰሃላና አበርገሌ ወረዳዎች የማሾ ሰብል በሰፊው እየለማ መሆኑን ጠቁመው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የማሾን ምርታማነት ለማሳደግም ከሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር ሰብሉን በስብጥር በመዝራት ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል የምጣኔ ሃብትና ግብርና ስርፀት ተመራማሪ አቶ አደመ ምህረቱ እንደገለጹት፤ በቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ የማሾ፣ ሰሊጥና እንቁ ዳጉሳ የሰብል ዝርያዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው።


 

ማዕከሉ በቆላማ አካባቢዎች ማሾን ከእንቁ ዳጉሳና ቦለቄ ጋር አሰባጥሮ የመዝራት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል።

በዝናብ አጠር አካባቢዎች የማሾ ሰብል ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ የሰሃላ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማስረሻ መኮንን ናቸው።


 

በቀጣይም እንደ ማሾ ያሉ ሰብሎችን በስፋት በማልማት በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት በምርምር የታገዘ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በዝቋላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጅንን ገብሬ፤አንድ ሄክታር የእርሻ መሬታቸውን በማሾ ሰብል ማልማታቸውን ተናግረዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በ2017/18 የመኸር ወቅት ከ120 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም