ችግሮች በሀገራዊ ምክክር እንዲፈቱ ድጋፋችንን ይበልጥ እናጠናክራልን -የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮች በሀገራዊ ምክክር እንዲፈቱ ድጋፋችንን ይበልጥ እናጠናክራልን -የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዳማ፤ ሕዳር 9/2018(ኢዜአ)፡- የተቃርኖ ሃሳቦችን በማስታረቅ ችግሮች በሀገራዊ ምክክርና ውይይት እንዲፈቱ ድጋፋቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
በዓለም ላይ ብዙ ሀገራት ችግሮቻቸውን በውይይት በመፍታትና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያም እንዲሁ ችግሮቻን እየፈታች ብትመጣም አሁንም መሻገር ያልተቻሉ ጉዳዮች በመኖራቸው በምክክርና በውይይት መፍታት ያስፈልጋል።
ለዚህም ለተቋቋሙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውውን መወጣት ይጠበቅበታል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ቆይታ አደርጓል።
የኩሽ ሕዝቦች ብሔራዊ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት አቶ ማንአይቶት በየነ በሰጡት አስተያየት፤ እንደ ፓርቲያችንም ሆነ እንደ ዜጋ ችግሮቻችን መፍታት የምንችለው በምክክር ብቻ እንደሆነ እናምናለንብለዋል።
ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ የምክክር ኮሚሽኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፍ በማድረግ በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።
ካልተነጋገርን ችግሮች መፍታት አንችልም ያሉት አቶ ማንአይቶት፤ ሁሉን አካታችና አሳታፊ የሆነ የምክክር በማካሄድና የተቃርኖ ሀሳቦቸን በማስታረቅ ችግሮቻችን በዘላቂነት መፍታት አለብን ነው ያሉት።
የሀገራችን ዜጎች፣ ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ ማሕበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሮችን ለመፍታት በውይይት፣ ንግግርና ምክክር አለመግባባቶችን መፍታት ይኖርብናል፤ ለዚህም ድጋፋችንን እናጠናክራለን ሲሉ ገልጸዋል።
መንግስት የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋምና ወደ ተግባር እንዲገባ በማድረጉ እናመሰግናለን ያሉት አቶ ማንአይቶት፤ በእስከ አሁኑ ሂደት እስከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል ድረስ በመውረድ ሕዝቡንና ፓርቲውን ይወክላል ያልናቸውን ስምንት አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ አስረክበናል ብለዋል።
የጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ /ጎጎት/ ሊቀመንበር አቶ ሙሐመድ አብራር በበኩላቸው፤ ችግርችን ከመሰረቱ ለመፍታት ምክክሩ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ምክክሩ የተቃርኖና የፖለቲካ ፍላጎቶች ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሮችና ቅራኔዎችን ለመፍታት በሀገራዊ ምክክሩ የምናገኛቸውን እድሎች መጠቀም አለብን ያሉት አቶ ሙሐመድ፤ ለዚህም የፓርቲያቸው ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በአጀንዳ አሰባሰብ ወስጥ መሳተፋቸውን ያወሱት አቶ ሙሐመድ የምክክር ውጤቱ የተሳካ እንዲሆን በትብብር እንሰራለ፣ ፍፁም ሰላማዊና ሕጋዊ የሆነ የፖለቲካ ትግል ብቻ አማራጫችን መሆን አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰሞኑን ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት ማካሄዱ የሚታወስ ነው።