ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ ዓለም አቀፍ መሪ ለመሆን በቁርጠኝነት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ ዓለም አቀፍ መሪ ለመሆን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለፁ።

14ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤዳኦ አብዲ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ምርት ማምረት የሚያስችል አቅም አላት።

በዚህም ኢትዮጵያ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ ዓለም አቀፍ መሪ ለመሆን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።

ይህን እምቅ አቅም ለመጠቀም መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ገበያዎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ፣ በገበያ የሚመራ የምንዛሬ ተመን መቀበል፣ እንዲሁም የዋጋ ተመን ማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።


 

የንግድ ስርዓትን ማቅለል እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ተወዳዳሪነት፣ ጥራትና ብዛት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንዳለ ጠቅሰዋል።

ይህም ምርታማነትን ለማሻሻል፣ የእሴት ሰንሰለትን ለማሳደግ እና አምራቾችን ጨምሮ ለገበያ ተዋናዮች የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት አይተኬ ሚና አለው ነው ያሉት።

በቅርቡ ወደ ተግባር የተገባው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለዘርፉ ተዋንያን አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ይፈጥራል ነው ያሉት።

እንዲሁም የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተደረገ ላለው ሂደት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው፤ በመንግሥት የተሰጠው ትኩረት የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ዘርፍ ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲያስመዘግብ አስችሏል ብለዋል።


 

በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ማሻሻያዎች ለዘርፉ እድገት አይተኬ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በቀጣናው እና ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ለመሳተፍ አቅም መፈጠሩን አንስተው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲሁም የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።

የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት በአፍሪካ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጥምረቱ የቦርድ ሰብሳቢ ሀይለማርያም ደሳለኝ ናቸው።


 

የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች እየጨመረ የመጣውን የዓለም ፍላጎት ለማሟላት ወሳኝ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች በአፍሪካ ውስጥ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኃይል ለመሆንና ኑሮን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎችን በማምረት ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

የመንግስት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ በመሆን በአፍሪካ ለቅባት እህሎች እና ጥራጥሬ እሴት ሰንሰለት ዕድገትና ሽግግር እያደረጉት ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት በአፍሪካ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም