ቀጥታ፡

የመንግስት የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ያለው በመሆኑ ያለምንም ልዩነት ለተግባራዊነቱ አብረን እንሰራለን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ የመንግስት የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ያለው በመሆኑ ያለምንም ልዩነት ለተግባራዊነቱ አብረን እንሰራለን ሲሉ የሃይማኖት አባቶችና አባ ገዳ ገለጹ፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የየካ ክፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ዋና ሰብሳቢ መልዓከ-ኃይል አባ ኃይለገብርኤል ከተማ ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችው እድገቷን እንደ ስጋት በሚመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶቿ ሴራ እና በወቅቱ በነበሩ መሪዎች ቸልተኝነት መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንደነበረች ታሪካዊ ማስረጃዎችን በመጥቀስ፤ የባህር በርን መመለስ የፍትህ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችው የባህር በር በእውነት ይመለሳል፤ የእውነት ጊዜው ደግሞ አሁን ነው ብለዋል፡፡

የመንግስት የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ያለው በመሆኑ፤ ያለምንም ልዩነት ለተግባራዊነቱ አብረን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ሸሪፍ በበኩላቸው፤ በአሻጥር የሄደውን የባህር በራችንን በሰላም እናስመልሳለን ብለዋል፡፡

መንግሥት የባህር በራችንን ለማስመለስ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፤ የአሁኑ ትውልድ የባህር በርን የማስመለስ አደራ እንደተጣለበት በመረዳት ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት በማለት አስገንዝበዋል፡፡

እኛ የሃይማኖት አባቶች የባህር በርን በማስመለስ ሒደቱ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ያነሱት ደግሞ አባ ገዳ ወልደአብ ገብረአብ ናቸው፡፡

እነዚህ ለውጦች የተመዘገቡት መንግስትና ህዝብ በጋራ መስራት በመቻላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ የባህር በር ለማስመለስ በሚደረገው እንቅስቃሴም እንደ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንቆማለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም