ቀጥታ፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ፌዴራሊዝምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል

ጅግጅጋ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ፌዴራሊዝምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ያለው ሚና የጎላ መሆኑን የሱማሌ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ፋራህ አብዲላሂ ገለጹ።

የሱማሌ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች 20ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ’’ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ በጅግጅጋ እያከበሩ ነዉ።

የሱማሌ ክልል ምክር ቤት ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ይኸው መድረክ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞችን ያሳተፈ የፓናል ውይይት፣ ሲምፖዚየምና የደም ልገሳ መርሃ ግብሮችን ያካተተ ነው።

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ፋራህ አብዲላሂ እንደገለጹት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የፌዴራሊዝም አስተምህሮን በማጎልባትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።


 

በመድረኩ በፌዴራሊዝምና ህገ መንግስቱ ላይ ሰፊ ገለጻ በማድረግ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኛን እይታ በማስፋት ክልላዊ ብሎም ሀገራዊ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጉላት እንደ ዓላማ ተይዟል ብለዋል።

የሠራተኛውን እይታ በማስፋትና የእርስ በርስ ትስስርን በማጠናከር ሰራተኛው የአገልጋይነት መንፈሱን የሚያሳድግበት መድረክ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ያስመረቅንበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት አቶ ፋራህ፤ ዓመቱ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት መሰረት የተጣለበትና የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመን የተጀመረበት መሆኑንም ገልጸዋል።

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም