በኦሮሚያ ክልል የዲጂታል ጤና አገልግሎትን የማስፋት ተግባር እየተከናወነ ነው - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የዲጂታል ጤና አገልግሎትን የማስፋት ተግባር እየተከናወነ ነው - ቢሮው
አዳማ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የዲጂታል ጤና አገልግሎትን በሁሉም የህክምና ተቋማት በማስፋት ቀልጣፋ ህክምና ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በግልጽ እንደተመላከተው የመንግስት አገልግሎቶችን በማዘመን የዲጂታል ጤናን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶን ማስፋት አንዱ ተግባር ነው።
የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ ሲስተሞችን ማበልጸግ፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን(ICT) መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት፣ የዲጂታል አስተዳደርን ማስፈን እንዲሁም የአሰራር ስርዓት በማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበር ዋና ዋና ስራዎች ናቸው።
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው ለኢዜአ እንዳሉት የዲጅታል ጤና ስርዓት የጤና አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ጥራቱን የጠበቀና አስተማማኝ ማድረግ ያስችላል።
ለዚህ እውን መሆን በክልሉ በተመረጡ ሆስፒታሎች ከወረቀት ነፃ የሆነው የዲጂታል ጤና አገልግሎት በፓይለት ደረጃ ተተግብሮ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ግልጽ፣ ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ እና እንደ ሀገር ለተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ እየከፈተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ደረጃ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የቢሾፍቱ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ታደሰ ጎንፋ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ለሶስት ሚሊዮን ህሙማን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው ሁሉም ዓይነት የህክምና አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ አድርገናል ብለዋል።
ይህም የታካሚዎችን እንግልት በመቀነስ ተገልጋዮች በቀላሉ ከሐኪሞቻቸው ጋር እንዲናበቡ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል ነው ያሉት።
የዲጂታል ጤና አገልግሎቱ መተግበር ለህሙማን ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረጉም ባሻገር የተገልጋዮችን እንግልት ቀንሷል ያሉት ደግሞ የጊኒር አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ኑር ዛላም ናቸው።
ዲጂታል ጤና በዘመናዊ አሰራር ለውጥ እያመጡ ካሉ ግንባር ቀደም ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረው የዲጂታል ጤና ስርዓት መዘርጋቱ አገልግሎቱን ቀልጣፋና ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል።